ሌላ ፍጥጫ

  |   Written by   ታመነ መንግስቴ   |   ሕብረተሰብ / social

ሰሞኑን ኢትዮጵያ በእያቅጣጫው ተወጥራለች።ኮሮና እንደ ዓለም ወሯታል-አካሄዱ ያባባል።ግብፅ ያዙኝ ልቀቁኝ እያለች ነው።አገር ውስጥም ህወሃትና ብልፅግና "ነይልኝ"-ነይልኝ መባባል ጀምረዋል።ፍጥጫ በርክቷል።

ሌላው ፍጥጫ ወዲህ ነው።በነጫጮቹ አቆጣጠር 2016 የአፍሪካ በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ማዕከል በምህፃሩ CDC ትልቅ ህንፃ ሊገነባ አሰበ።ለዚህም ገንዘቡን ቻይና ፣መሬቱን ኢትዮጵያ ሊችሉ የመግባቢያ ስምምነት ተፈርሞ ባለፈው የ2020 የካቲት መግቢያ ላይ የመሠረት ድንጋይ በአፍሪካ መዲና አዲስ አበባ ተጣለ።

ይሄን የሠሙ የኢትዮጵያ ከፍታ የሚያሳንሳቸው ትንንሽ አገራት የCDC መዲናነቷን ተቃውመው ከሰሞኑ ተነስተዋል።በዓባይ ጉዳይ ላይ ብዕር የሚማዘዙ የአገር ልጆች ጉዳዩን እንደተጨማሪ ጦርነት ሊያዩት ይገባል።ምክንያቱም ድሉ የጥቁር ህዝቦችን አገናኝ አገር ኢትዮጵያ ዳግም ትንሳኤ የሚያፋጥን ነውና።

ቻይና 80ሚሊዮን ዶላር ሆጭ አድርጋ ልትገነባው የመሠረት ድንጋዩ የተቀመጠለት የCDC አፍሪካ ህንፃ ብዙ እያንጫጫ ነው።ነገርዮሹ ከአፍሪካ ደቡብ አፍሪካንናሞሮኮን የኢትዮጵያ ተቀናቃኞች አድርጓል።የማንዴላ አገር ጠንከር ብላ ከኢትዮጵያ ጋር እንዳትፋለም ከሞሮኮ ጋር ባላት ፍቅር አትተማመንም የሚለው የዴይሊ ማቬሪክ ድረ ገፅ ዘጋቢ ነገር ግን የህንፃውን ግንባታ ለማስተጓጎል እየተውተረተረች መሆኑን ገና በርዕሱ ያስረግጣል።

አረባዊት የአልሞሃድና አልሞራቪዶች እምብርት ሞሮኮ ህንፃው እኔ ዘንድ ቢገነባ የተሻለ ሊራቀቅ የሚችልበት አቅም አለኝ እያለች ሲሆን በምዕራባዊት ሰሃራ ነፃ መሆን አመካኝታ ከአፍሪካዊያን አንጡራ ድርጅት-አፍሪካ ህብረት ዘልላ ወጥታ ሲመቻት መመለሷ በሰሃራ በታች ሰዎች የተረሳላት አይመስልም።

በጣጣው ውስጥ አሜሪካና ቻይና በእጅ አዙር ተፋጠዋል።የትራምፗ ዋሽንግተን ለCDC "አለሁለት" እያለች ቢሆንም የሩቅ ቅርቧ ቻይና ደግሞ "ለድሃ አፍሪካዊያን በጃክማ በኩል የኮሮና መመርመሪያ እና መተንፈሻ የኢትዮጵያ አየር መንገድን አሸክሜ የደረስኩላቸው ፈጥኖ ደራሻቸው ነኝ" ስትል መልስ መታለች።

በዚህ በኩል በቻይና የተረቱት አሜሪካዊያንና ግብረ አበር የአፍሪካ እንደራሴዎች(Diplomats) "ቻይና በህንፃው ላይ ድብቅ መሠለያ ገንብታ እየቀረፀች የመድሃኒት መፈልሰፊያ ታደርገዋለች" ሲሉ ይከሳሉ።መድሃኒት መፈልሰፍ የሰይጣን ስራ ባይሆንም በአፍሪካ ህብረት አዳራሽ ላይ የሆነውን ያዩ አፍሪካዊያን ይሞኛሉ ማለት የሞኝ ሰበብ ነው።

ነገሩን ከነገር ጋር ለማገናኘት እንዲህ ያሉ የአፍሪካን መቀመጫነት ከሺህ -አገር(ሸገር) የመቀማት ሴራዎች ብዙ ነበሩ።አፍሪካን ከገባችበት የቅኝ ግዛት ግዞት መንጥቀው ካወጧት ልጆቿ አንዱ ቀኃሥና የአገራቸው ልሂቃን ከተማ ይፍሩ እንዲሁም የዛሬው የመረብ ማዶ የዚያኔው የመረብ ወዲህ ሰው ተስፋየ ገብእዝጊ ትግል አህጉሪቱን ሰፍቶ ምሰሶዋን ኢትዮጵያ ላይ መስርቶ ዛሬ አድርሷታል።

እነሱ ያቆሙትን መሠረት ነቅንቀው ዋና ዙፋኑን ወደ አገሮቻቸው ሊወስዱ የቋመጡ የአፍሪካ አገራት በበረከቱ ጊዜ ታሪክ ያደረሳቸው የያኔው መራሄ መንግስት መለስ ዜናዊ ተገኙ።

እሳቸው ከአዛዥ(General) ዊንጌት ትምህርት ቤት ጀምረው ባካበቱት እንግሊዝኛ"ማንዴላን ያስተማረው ማነው?---ሙጋቤን አይዞህ ያለው ማነው?"እያሉ በማፋጠጥ እነ ጋዳፊን ጭጭ አሰኟቸው።አፍሪካ ህብረትእንደመጣ ከተወለደበት ሳርቤት ሰፈር ጠና።ዐቢይ የአባቱን የቀኃሥን ሃውልት ደጁ ላይ አቁሞ-የአፍሪካን ልጅነት አስረገጠ-እሱም ታሪክ ሰራ።

መዲናነቱ ስለሚሰጠን ጥቅም ከምወሸክት ተገቢ ነን ወይ? ስለሚለው አውግተን እንለያያለን።እጅግ በጣም ተገቢ ነን።

ዘፍጥረት የሚያውቀው የአፍሪካ አገር ኢትዮጵያ ብቻ ነበር።ግብፅ አፍሪካ ላለመሆኑ ምስክሩ ብዙ ነው።መልኩ፣"የግብፅ አረባዊት ሪፐብሊክ" የሚሰኝ ስሙ በቃ ብዙ።እናም ከኖህ ልጆች አንዱ ካም ወደ አፍሪካ ሲመደብ ባድማው ኢትዮጵያ ነበረች።

ከዚያም ወዲህ ጥቁሩ ዓለም በባርነት ወድቆ ተስፋ በነጠብጣብ ይቀጣጥል በነበረ ጊዜ አንዲት ለዘመናት ነፃ የሆነች የጥቁሮች ደሴት ሲፈልግ ያገኘው ኢትዮጵያን ነበር።ኢትዮጵያኒዝም የሚባል ማህበረ ዱኛ(ፖለቲካ) እና ራስተፈሪያኒዝም የተሰኘ ሃይማኖት አርማዎቹ ኢትዮጵያና ቀኃሥ ነበሩ።ቀኃሥ የራስታዎች አምላክ መሆናቸው ተፅፎ በቅቶታል።

ስለሆነም ኢትዮጵያ ለመዲናነት ተመራጭ የሺአገር የሆነች ከተማ ስላለቻት እንኳንስ የበሽታዎችን መቆጣጠሪያ መስሪያ ቤት ቀርቶ የምድርን ልብ ምት መቆጣጠሪያ ቢመሰርቱባት ትችላለች።

በተፈጥሯቸው ለድርጅቶች መቀመጫነት ስልታዊ የሆኑ ከተሞች አሉ።ሲውትዘርላንድ የምትባልን ጤፍ የማታህል አገር ሳያውቅ ዠኔቭን የጠነቀቀ ሰው ብዙ ነው።ዠኔቭ እንደ አዲስ አበባ ተፈጥሮዋ የሰጠ ነው።

በመጨረሻም ያ ትውልድ ለሠጠን የመዲናነት ጥሪት እያደነቅነው የኔና የእናንተን ለመስራት ደግሞ በመረጃና ወሬ ጫጫታው ዘመን እንዳንበለጥ በዕውቀት እንታጠቅ።

የ#አመስጋኙ ትውልድ ቀላል ተግባር ያወቀውን ማጋራት ስለሆነ ከዚህ በታች የተጠቀሰውን ማስፈንጠሪያ እያነበባችሁ ለወዳጆቻችሁ አድርሷቸው፤ተወያዩበት፣ፃፉበት፣ ሞግቱበት።

ያነሳሳኝን መምህር ሃብታሙ አለማየሁን አመስግኘ ማስፈንጠሪያውን የማጋራችሁ ድረገፅ የመረጃ ምንጨ መሆኑን ገልጨ ልሰናበት!

https://www.dailymaverick.co.za/article/2020-06-09-sa-urged-to-stop-china-building-africa-disease-control-centre-hq-in-addis-ababa/amp/