~ አሁን ደግሞ የሠዓልያኑ ተራ ነው የተዋሕዶ ልጆች ሆይ ተገለጡ !!

  |   Written by   Zemedkun Bekeles posts   |   ሕብረተሰብ / social
~ አሁን ደግሞ የሠዓልያኑ ተራ ነው
የተዋሕዶ ልጆች ሆይ ተገለጡ !!
*~★★~*
• ደፈር ብለን ነጭነጯን ለመነጋገር ሠዓልያን እንሰባሰብ።
• ጦማሩ #BLOCK አለው። የግል ጉዳይ ስለምናወራ የማይመለከታችሁ ተደበቁ። ቀስፌህ የወሬ ጠኔ እንዳይደፋህ ጮጋ ለማለት ሞክር። በተለይ ወሄ ሰምተሃል።
#ETHIOPIA | ~ “በዚያ ቀን የወደቀችውን የዳዊትን ድንኳን አነሣለሁ፥ የተናደውንም ቅጥርዋን እጠግናለሁ፤ የፈረሰውንም አድሳለሁ፥ እንደ ቀደመውም ዘመን እሠራታለሁ፤” አሞ 9፥11
•••
“በማዕዶት ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ የትናንቱን ለነገ ማኅበራችን ” በኩል በይፋ በቀረበ ጥሪ መሠረት እስከአሁን ድረስ በመላው ዓለም የሚኖሩ፦
• አርክቴክቸሮችና ኢንጅነሮች
• የአይቲ ባለሙያዎች
• የሕግ ባለሙያዎች
• የህክምና ባለሙያዎች
• የኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ተሰባስበው መመካከር፣ መወያየት፣ ዕቅድ ማውጣት ጀምረዋል። አሁን ተራው ዛሬ ደግሞ የሠዓልያን ነው። የኢትዮጵያውያን ሰዓልያን። እናስ ሠዓልያን ከወዴት አላችሁ? ብቅብቅ በሉ።
•••
የትናንቱን በዛሬ ላይ ለነገ እናስተላልፍ ዘንድ መሰባሰባችን የግድ ነው ብለን ቆርጠን መነሣታችንን ዓለሙ ሁሉ ከሰማና ካወቀ ሰንበትበት ብሏል። ምንም እንኳ በራሳችን እንዝህላልነትና ቸልተኝነት እንደ ጥቁር አሜሪካዊው ሟች ጆርጅ ፍሎይድ ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን አንገት ላይ ቋሚው ቢበዛም እስከዛሬ ሳንሞት፣ እያጣጣርን ደግሞም እነተጫኔን እያሽቀነጠርን፣ ከላያችን ላይ እያራገፍን በብዙ መከራ መሃል፣ በድቅድቅ ጨለማና በሞት ሸለቆም ውስጥ ሆነን ከዋሻው ጫፍ ወደሚታየው የሚደንቅ ብርሃን ወደ መሸጋገሩ እያመራን ነው።
•••
ገዳይ ዮዲት ጉዲትን አራግፈናት፣ የቱርክ ቡችላውንና ገዳዩን ግራኝ አህመድን ታሪክ አድርገን፣ ደርቡሽና ጣልያንን፣ ቱርክና እንግሊዝን ደርግንም፣ ህወሓትንና ኃይለማርያምንም ሸኝተን አሁን ደግሞ በአቢቹና ታኬ ዘመን እየሞትን፣ እየተቃጠልንም ቢሆን እንዳለን አለን። ሁላቸውም እንደቀደሙቱ ታሪክ ይሆናሉ። ጋሽ ታከለና የጋሽ አቡቹ መንግሥትም እንደ ቀደምቶቹ ድራሹ ይጠፋል። ቤተ ክርስቲያን ግን ትኖራለች። እነሱ መቃብር ላይ ሰንደቅ ዓላማዋን ተክላ ትቀጥላለች። በተለይ ከልብ በመነጨ እውነተኛ ፍቅር ከተሰባሰብን፣ ከተዋደድን፣ ይቅር ለእግዚአብሔርም ከተባባልን፣ ንስሐም ከገባን፣ የኢትዮጵያ ሀገራችንም ሆነ የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን ትንሣኤ ቅርብ ነው የሚሆነው። ቅርብ እዚህ ከአፍንጫችን ስር።
••• እንግዲህ ሠዓሊ ስማኝ ልንገርህማ ! ይህቺን ፦
• ነፃነት ከነክብሩ፥
• ሙሉ ትምህርት፥
• ሕግን ከነ ሥርዓቱ፥
• አንድነት ከነጀግንነቱ፥
• ኪነ ጥበብ በየዓይነቱ፥
• ሥነ ጥበብ በየመልኩ፥
• ታሪካዊና ጥንታዊ ቅርስ፥
• ሰንደቅ ዓላማን ከነ ክብሩ፥
• ስም ከነምልክቱ ከነ ትርጉሙ፥
• አገር ከነ ዳርድንበሩ፣ ከነፍቅሩ፥
• ዜማን ከነመሳሪያው ከነምልክቱ፥
• ሥነ ጽሑፍ ከነጠባዩ፣ ከነሙያው፥
• እምነት/ ሃይማኖትን ከነፍልስፍናው፥
• ፍጹም ቋንቋን ከነፊደሉ፥ ከነቁጥሩ ከነትውፊቱ፦
… ፈጥራ፣ አምጣ ወልዳ አሳድጋና አዘጋጅታም ለዓለም ያበረከተች፤ ለእኛ ለኢትዮጵያውያንም ያስረከበች ዕጹብ ድንቅና ከ ሀ እስከ ፐ እንከን የሌለባት፣ ኢትዮጵያንም ጠፍጥፋ አሁን ያላትን ቅርፅ ይዛ እንድትወጣ አድርጋ የፈጠረች፣ የሠራቻትን ቤተ ክርስቲያንህን ክብሯን ለመመለስ ተነሥ። ሸራህን ወጥር። ቀለምህን በጥብጥ። ቡሩሽን አዘጋጅ።
•••
ስማኝ ሠዓሊ ቤተ ክርስቲያንን የማይወክሉ የሆልዩድ አክተሮችን ፎቶ፣ የጣልያንና የህንድ አክተሮችን ፎቶ፣ የሚል ጊብሰንንና የሌሎቹንም የአማሪካና የቻይና ተዋንያን ፎቶ ከተዋሕዶ ልጆች አእምሮም፣ ጓዳና ጎድጓዳም መንጥረን እናስወግድ ዘንድ የእናንተ መሰባሰብ የግድ ነው። የግድ። ተሰባሰቡ።
•••
እኛ ኢትዮጵያውያን ነን። የራሳችን የሥነ ሥዕል ጥበብ የምንጠቀም ኢትዮጵያውያን። የአሣሣል ዘይቤአችን ትርጉም ያለው። ሥዕሉ በራሱ እንደ መጽሐፍ የሚነበብ። የራሳችን ከለር ያለን ህዝቦች ነን። መቀላወጥ አያስፈልገንም። በየት በኩል እንደገባ የማናውቀው የፈረንጅ አክተሮች ሥዕልም አያስፈልገንም። ይሄ ሁሉ የጋራ ጥፋታችን ነው። ሃይ ባይ ተቆጣጣሪ ይሁነኝ ባይ ግድ የሚሰጠው ወሳኝ አካል ስለሌለ ነው። እናም አሁንም አልረፈደም። ወደ መጪውም ትውልድ ሳይተላለፍ በአጭሩ ልንቀጨው ይገባናል። የሆልዩድ አክተሮችን ፎቶ ከቤተ ክርስቲያን፣ ከምዕመናን ጓዳም አጥፍተን በራሳችን በቀደሙ ቅዱሳት ሥዕላት እንተካ ዘንድ ጊዜው አሁን ነው። አሁን።
•••
እናም አባዬ አትልመጥመጥ፣ አትኩነስነስ፣ አትጀባነን፣ በባዶ ሜዳም አትንቦጣረር። ፀጉርህን አትፍተል። ተነሥ፣ ወስን፣ ወስንና፦
• ሙሉ ስምህን
• ሙያህን
• የሥራ ልምድህን
• ስልክህን
• የመኖሪያ ከተማህን ሞልተህ በውስጥ መስመር ላክልኝማ። ከዚያ ልክ እንደሌሎቹ ወንድም እህቶችህ አንተም በቴሌግራም ትሰባሰብና እየመከርክ፣ እርስበእርስ እየተዋወቅክ ትቆያለህ። ይኸው ነው። በኢትዮጵያ፣ በአፍሪካ፣ በአውሮጳ፣ በአሜሪካ፣ በካናዳ፣ በእስያ፣ በዐረቡ ዓለምና በአውስትራልያ የምትኖሩ ኢትዮጵያውያን የሥነ ሥዕል ባለሙያዎች ተሰባሰቡ። እንሰባሰብ።
•••
ቀጣይ ተረኛ ተዘጋጅተህ፣ በተጠንቀቅ ጠብቅ።
•••
ሻሎም ! ሰላም !
ዘመድኩን በቀለ ነኝ።
ግንቦት 24/2012 ዓም
ከራየን ወንዝ ማዶ።