ኮሮና የረሳት የመን

  |   Written by   ታመነ መንግስቴ   |   ጉዞ / Travelዐለም በጋራ "ውጭ ነፍስ ግቢ ነፍስ" ውስጥ ባለችበት በዚህ ምፅዓት የመሠለ ጊዜ ውስጥ ያች ከአምስት ዓመታት በፊት ጀምራ በሃውቲ አማፂያንና ገንዘብ ባደደባት ሳውዲ አረቢያ ስትታመስ የነበረችው አገረ የመን በኮሮና ተዘንግታለች።


ኢትዮጵያውያን አፄ ካሌብ በሚሉት ሃያል ንጉሳቸው አማካኝነት ቀዩን ባህር ተሻግረው ለአምሳ ዓመታት ያህል ሲያስገብሯት "ናግራን" የሚል ስም አውጥተውላት የነበረችው የመን፤በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ነድዳ እየከሰለች እና እግዜሩ የረሳት በመሠለበት በዚህ ወቅት ከጅምላ ጨራሹ ወረርሽኝ ነፃ አገር መሆኗ አጃኢብ ያሰኛል።


ነገሩን ከነገር ጋር ለማገናኘት ያህል እንደ የመን ያሉ ዓለሙ የዘነጋቸው አገራት በሰሞነኛው የጋራ ጠላት ኮሮና ተህዋሲ ሳይጠቁ የተገኙ ሲሆን ለአብነትም በሳልቫ ኪርና ሪክ ማቻር ፍትጊያ ቋያ ሲነድባት፣ህፃናት ልጆቿ እንደ እንስሳ ቅጠል ሲበሉ የታዩባት ደቡብ ሱዳን ከኮሮና ነፃ ነን ከሚሉ በአንድ እጅ ጣት ከሚቆጠሩ የፈለካችን አገራት አንዷ ሆና ትጠቀሳለች።


በደግነታቸው ከኢትዮጵያዊያን ይበልጣሉ ሲል አሁን በበለፀገው ኢህኣዴግ አማካኝነት በሙያው የተነሳ ማጎሪያ ቤት  ከመግባት አምልጦ በዚያች አገር ለዓመታት የኖረው ነገራተሰብ(ጋዜጠኛ) ዳንኤል ገዛኸኝ በፃፈው "ሲዋን" የተሰኘ አስደናቂ የጉዞ ማስታወሻ ላይ የመሠከረላቸው የመናዊያን የእኛ አገር ከርታታ ስደተኞች መሻገሪያ መሆናቸውን ልብ ይሏል።


ስለ ደግነታቸው ዳንኤል ገዛኸኝ በነገረን ምስክርነት ለመሰናበት"---መቼም ገንዘብ የለንም።አንድ የተረዳነውና ያወቅነው ነገር የመንና የመናዊያን ከእኛ አገር ሰው የበለጠ ከሚነገርላቸው በላይ እንግዳ ተቀባይ መሆናቸውን ነው።" የመናውያን እንዲህ ናቸው-የኔ እግዚያብሔር የነሱ አላህ ያድናቸው!!!


።፨፨፨፨።፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨

ይቆየን!