አንገብጋቢው ጉዳያችን -ኮሮና

  |   Written by   ረድኤት የኔነህ   |   ሕብረተሰብ / socialበኮሮና ቫይረስ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር በየሰአቱ እያሻቀበ ነው።በጣሊያን በየቀኑ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሞቱ የሚለው ዜና መጀመሪያ ላይ ሁሉንም ጉድ ቢያስብልም አሁን ግን አስደንጋጭነቱ ቀንሶ የተለመደ አይነት ዜና ሆኗል።አሁን ደግሞ ስፔናውያን ይንኑ አሃዝ የሚስተካከል የሞት መጠንን በማስመዝገብ ላይ ይገኛሉ።በአሜሪካ የሟቾቹ ቁጥር አንድ ሺህ ማለፉም ፣ቫይረሱ የአለምን ህዝብ ቀስ በቀስ ወደ መቃብር ሸኝቶ ምድሪቱን ባዶ እንዳያስቀራት አስግቷል።


ሀገራት ቫይረሱን ለመቆጣጠር ህዝቦቻቸውን ከቤት እንዳይወጡ ከማስጠንቀቅ አልፈው አሁን ላይ ወደ ማስገደዱ ተሻግረዋል።ከ8 ሺህ በላይ ዜጎቿን ያጣችው ጣሊያን በሀገሪቱ ማንም ሰው በጎዳናዎች ላይ እንዳይታይ ብለው ያወጡትን ህግ  በሰው አልባ አውሮፕላኖች ጭምር በመታገዝ አፈጻጸሙን እየተከታተሉ ይገኛሉ።


የአለም ጤና ድርጅት ቀጣዩ ቫይረሱ ክፍኛ የሚያጠቃት ሀገር አሜሪካ ልትሆን እንደምትችል ማስጠንቀቂያ አዘል መልዕክቱን አስተላልፏል።ልዕለ ሀያሏ ሀገር ቀደም ሲል ቫይረሱ በቻይና ሲከሰት እምብዛም እንደማያሰጋት በፕሬዚዳንቷ በኩል ስታስተጋባ ከርማ አሁን ግን ከ 1ሺህ በላይ ዜጎቿን በሞት ስታጣ" ሰርገኛ መጣ..." አይነት ሩጫዎችን ጀምራለች።ሌላው የሚገርመው ነገር በአሜሪካ በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር 85 ሺህ የመድረሳቸው ዜና ነው።ይህ ቁጥር  በየቀኑ በአማካይ ከ600 በላይ ዜጎቿን እያጣች ከምትገኘው ጣሊያን እንኳ በ5ሺህዎች የሚበልጥ ነው።


ኮሮናን "የቻይና ቫይረስ"እያሉ በመጥራታቸው ከአለም ጤና ድርጅት ሳይቀር ተቃውሞ የገጠማቸው አወዛጋቢው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ፡ትናንትና ደግሞ በርካታ የቫይረሱ ተጠቂዎች በሀገሮ መገኘቱ ላይ ምን የሚሰጡት ሃሳብ አለ ተብለው በጋዜጠኞች ሲጠየቁ -እኛ ብዙ ሰዎችን በመመርመራችን ነው ቁጥሩ የበዛው፣ሌሎች ሀገራት አንደኛ ዜጎቻቸውን ቢመረምሩ ከኛ የበለጠ የተጠቂ ቁጥር ያስመዘገቡ ነበር በማለት ተናግረዋል።


በሌላ በኩል ደግሞ በአውሮፓ በሞት መጠን ሁለተኛ ደረጃን የያዘችው ስፔን በወርሽኙ እንደዚህ ለመጠቃቷ ትልቁ ምክኒያት እግርኳስ ነው ሲሉ የጣሊያኗ ቤርጋሞ ከተማ ከንቲባ ለ ጋርዲያን መናገራቸው ግርምትን አጭሯል።በፌብርዋሪ ወር የስፔኑን ክለብ ቫሌንሺያንና የጣሊየኑን አትላንታ ያገናኘው የሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ ላይ 40 ሺህ የአትላንታ እና 2500 የእንግዳው ቡድን ቫሌንሺያ ደጋፊዎች መታደማቸው ተገልጿል።እንደ ከንቲባው ገለጻ ከጨዋታው በኋላ የተመለሱት ስፔናውያን ደጋፊዎች ቫይረሱን በቀላሉ በሀገራቸው አስፋፍተውታል ይላሉ።የሰውየውን ንግግር እውነት ነው ብለን እንድንቀበለው የሚያስገድደን ነገር በስፔን በኮሮና በመጀመሪያ የተያዙት የቫሌንሺያ ክለብ ደጋፊዎች እና ተጨዋቾች መሆናቸው በመረጋገጡ ነው።


ወደ ሀገራችን ስንመለስ መጋቢት 3 በአንድ ጃፓናዊ የጀመረው የተጠቂዎች ቁጥር ዛሬ ላይ 16 መደረሱ ይፋ ሆኗል።ቀስ በቀስ እየጨመረ የመጣውን የቫይረሱን ስርጭት ለመግታትም መንግስት የትምህርት ቤቶች መዘጋትን ከማራዘም በተጨማሪም ሊፈጠሩ ለሚችሉ አስጊ ሁኔታዎች ጡረታ የወጡና በትምህርት ላይ ያሉ የጤና ባለሙያዎች ለአስቸኳይ ግዳጅ ይዘጋጁ ብሏል።ነገር ግን አሁንም ድረስ ህዝቡ ጥንቃቄ የጉጎደላቸው ተግባራትን ከማከናወን አለመቆጠቡ እየታየ ነው።በተለይም ትላልቅ የገበያ ስፍራዎች አሁንም አለመዘጋታቸው ሀገሪቱን ስጋት ላይ ጥሏል።ፌደራል ፖሊስም የህዝቡ ቸልተኝነት በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ ሌሎች ሀገራት ላይ እየተደረገ እንዳለው ህዝቡን በሀይልም ቢሆን በቤቱ አርፎ እንዲቀመጥ ለማድረግ መዘጋጀቱን ተሰምቷል።እዚህ ላይ በማህበራዊ ሚዲያዎች ከተለቀቁ ቀልዶች መሀል"ኢትዮጵያውያን ከቤት እንዳትወጡ ቢባሉ ራሱ የወጣ ሰው አለመኖሩን ለማረጋገጥ በሚል ወጥተው ያያሉ"የምትለዋ የኛን ሀገር ሰው የምትገልፅ ናት።


ጤና ይስጥልኝ  !!!!