የስልኮቻችን ነገር በዚህ ጊዜ

  |   Written by   ረድኤት የኔነህ   |   ሕብረተሰብ / socialኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ከሚረዱን መንገዶች ውስጥ ይጠቀሳል -እጅን በተደጋጋሚ መታጠብ።ይህም የሆነው የሰው ልጅ ሁሉንም ተግባራት የሚያከናውነው በእጁ ስለሆነ ነው።ከዚህ በተጨማሪም 

በቤታችንም ሆነ በምንሰራበት ስፍራ በተደጋጋሚ የእጅ ንክኪ የሚበዛባቸው ስፍራዎችን ማጽዳት ከመከላከያ መንገዶቹ መካከል አንዱ ነው።

ነገር ግን ስልካችንን በየደቂቃው የምንጠቀም እንደመሆናችን እንዴት ማጽዳት እንዳለብን እስካሁን ካላሰብን ቀጣዩ ጠቃሚ ነጥብ ይሆናል።


ስልክዎን በኪስዎ፣ በቦርሳዎ አንዳንዴም ወደ በፀዳጃ ቤት ሲሄዱ ይዘውት ይሄዳሉ። ምን ያህል ጀርም ስልክዎ ብቻ ተሸክሞ እንደሚገኝ አስበውታል? ኮሮናንስ ስላለመያዙ ምን ያህል እርግጠኛ ነዎት?

የአሜሪካን የጤና ስርዓት በበላይነት የሚቆጣጠረው ሲዲሲ በምናስነጥስበት አልያም በምናስልበት ወቅት ከሰውነታችን የሚወጣው ጀርም በሚረጭበት ስፍራ ላይ ለሰዓታት በሕይወት ይቆያል ብሏል። ስለዚህ ቆሽሸው የሚታዩን ነገሮችን በአጠቃላይ እንድናፀዳ ይመክራል።

በማጽዳትና ከቫይረሱ ነጻ በማድረግ ረገድ ልዩነት እንዳለም ተቋሙ ያሳስባል። መጀመሪያ ቆሻሻውን ማጽዳት ቀጥሎም ከቫይረሱ ነፃ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ያስገነዝባል።


ስልካችንን ለማጽዳት 70 በመቶ አልኮል ያለው ዋይፐር መጠቀም የሚቻል ሲሆን በረኪና ግን አይመከርም። ቀላል ሳሙናና ውሃም ለማጽዳት እንደሚያገለግልም ባለሙያዎች ይመክራሉ።

ዶ/ር ሌና ሲሪክ በዩኒቨርስቲ ኮሌጅ ለንደን ማይክሮባዮሎጂስት ናቸው። እርሳቸው እንደሚመክሩት ከሆነ ስልክዎን ለማጽዳት ከቻርጀሩ መንቀል፣ መሸፈኛ ካለው ማውለቅ ቅድሚያ ልትወስዷቸው የሚገባው ተግባር ነው።


ዋና ዋና የሚባሉት የስልክ አምራቾች ስልካችንን ለማጽዳት ኬሚካሎች፣ ለእጃችን ማፅጃነት የምንጠቀምባቸው ሌሎች እንዲሁም ሸካራ ነገርን ለማጽዳት የሚያገለግሉ ዋይፐሮችን መጠቀምን አይመክሩም።

ለዚህ ደግሞ ምክንያታቸው የስልክዎን ስክሪን መከላከያ ይጎዳሉ አልያም ያወድማሉ የሚል ነው። ስለዚህ ይላሉ ዶ/ር ሌና፣ በቀላሉ በውሃና በሳሙና በተነከረ ጥጥ ወይም ከጥጥ በተመረተ ጨርቅ ማጽዳት በቂ ነው።

በጥጥ ወይም በጨርቁ የስልክዎን ስክሪንም ሆነ ጀርባ እንዲሁም ጎኖች ማጽዳት ይችላሉ። በዚህ ወቅት ግን የሚያጸዱበት ፈሳሽ በስልኮቹ ክፍተቶች በኩል እንዳይገባ ጥንቃቄ ያድርጉ።

በርግጥ አንዳንድ ውሃን የሚቋቋሙ ስልኮች ቢኖሩም ከጊዜ በኋላ ግን ይህንን ብቃታቸውን ሊያጡ እንደሚችሉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

በአግባቡ ከወለወሉ በኋላ በለስላሳ ጨርቅ ማድረቅ አይርሱ። ዶ/ር ሌና እንደሚሉት በሳሙናና ውሃ ስልክዎን ማጽዳት ቫይረሶችንና ጀርሞችን ከስልክዎት ላይ ያፀዳል።


አይፎንን ስልኮችን የሚጠቀሙ ከሆነ፣ አፕል ስልክዎን በአግባቡ 70 በመቶ አይሶፕሮፔል አልኮል ባላቸው ዋይፐሮች ማጽዳት እንደሚችሉ ይመክራል። እነዚህን ዋይፐሮች ከኮምፒውተር መለዋወጫዎች መሸጫ ሊያገኟቸው ይችላሉ።

በዚህ ሁሉ ስልክዎን ካፀዱ በኋላ ባልታጠበ እጅዎ ከሆነ የሚጠቀሙት መልሶ ስልክዎ በጀርሞች ይሞላል። ስለዚህ እጅዎን በየጊዜው መታጠብ አይርሱ!

              #ቢቢሲ አማርኛ

ጤና ይስጥልኝ  !!!