የኮሮና ጥቅሞች

  |   Written by   ታመነ መንግስቴ   |   ሕብረተሰብ / socialቢቢሲ የአማርኛው ዝግጅት ክፍል በገፀ ድሩ ከዘረዘራቸው የአስከፊው ወረርሽኝ "ጥቅሞች" መካከል፦የአየር ብክለት መቀነስ፣የመተላለፊያዎች ከሰዎች ጭንቅንቅ ነፃ መሆን፣የደግነት ተግባራት እየበዙ መምጣት፣በአንድነት የመቆም ስሜት ተዘርዝረው በመጨረሻ "የፈጠራ ችሎታ ማበብ" ተብሎም ተጠቅሷል።

ከፊት ያሉት አራቱ ይቆዩንና ወደ "ፈጠራ ችሎታ ማበብ" ስናዘግም ዛሬ ዓለም በየ ቤቱ ቆልፎ በተቀመጠበት እያንዳንዱ ሰው ከራሱ ጋር ንግግር የጀመረ ይመስላል።

ታሪክ እንደሚያስተምረን እንዲህ ባሉ የጭንቅ ጊዜያት የጀገኑ ሰዎች አዕምሯቸውን አሰርተው የቀጣዩ ዘመን አርበኛ ሆነው ኖረዋል።

ሁለተኛውን የዓለም ጦርነት አንስቶ እሷን መዘንጋት ነውር እስኪመስል የምናወሳት ትንሿ አይሁዳዊት ሴት አና ፍራንክ እንዲያ ያሉ አስደማሚ ሃሳቦችን "ኪቲየ" በምትላት ትንሽ ማስታወሻዋ ትታልን ያለፈችው በዚያ አስቀያሚ የጦርነት ወቅት በሆላንድ አገር በነበረች ድብቅ ማቆያ ለዓመታት ተቀርቅራ ነው።

እንዲያ ከትንሿ ብላቴና ይወጣሉ ብሎ ለማመን በሚቸግሩ ጥልቅ እሳቤዎቿ የጦርነቱን ፊታውራሪዎች እነ ሂትለርን ያስናቀችው ወጣት አዋዋሏ ከመፅሐፍት፣ሬዲዮ እና መፅሐፍት፣አሁንም መፅሐፍት ጋር እንደነበር በአስደናቂ የውሎ ማስታወሻዋ ከትባዋለች።

እናም ለአገሬ ወጣት ይሄን የድብርት ጊዜ ወደ መፅሐፍትና ፀሎት፣ራስን ወደ መመልከት እንመለስበት ዘንድ አሳስባለሁ።

ከዓመታት በሗላ ከሰሞኑ መፃፍ፣መሳል፣መቅረፅ፣መዝፈን፣መመርመር የጀመሩ ትጉ ኢትዮጵያዊያንን ታሪክ እንደምንሰማ ተስፋ አደርጋለሁ።

።፨፨፨።፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨
ይቆየን!