በእምነትና ጥንቃቄ መካከል

  |   Written by   ታመነ መንግስቴ   |   ጤና / fitness


ኢትዮጵያ ከዓለም ተለይታ እጆቿን ትዘረጋ ዘንድ የተፈቀደላት ቅድስት አገር፣የሶስቱም አብረሃም ላይ የተመሠረቱ ኃይማኖቶች(ይሁዲ፣ክርስትና፣እስልምና) አድባር መሆኗን የሚክድ ሰይጣን ብቻ ነው።

ስለዚህ ኢትዮጵያዊውን ከሚያምነው ፈጣሪው በልጦ ሊያድነው የሚችል ጥንቃቄ ባይኖርም ራሱን ፈጣሪውን መፈታተን ስለሚሆን መደረግ ያለበት ጥንቃቄ ቢደረግ መልካም ነው።

የፈጣሪን መኖር ክደዋል ብለን የምናማቸው ምዕራባዊያን እንኳን አለን በሚሉት ጥበብ ሁሉ ታግለው ሲሳናቸው"በምድር ያለውን ሁሉ አድርገን ስለተሸነፍን ወደ ሰማይ አንጋጠናል!" ሲሉ በጣሊያኑ መራሄ መንግስት ጁሴፔ ኮንቴ በኩል የተናዘዙለት አስከፊው የኮሮና ወረርሽኝ እኛን የሚምረን በፀሎትና ቀናነት የታከለበት ጥንቃቄ ነው።

ታሪክ አጣቅሶ በመፃፍ የማደንቀው በዕውቀቱ ስዩም በአንድ መጣጥፉ ላይ በጃንሆይ-አጤ ምኒልክ ዘመን ራሱን በበሽታ ስለጠረጠረ በማግለል ጫካ ገብቶ የንጉሱንና ህዝቡ ጤና ስለጠበቀ ሰው እንዲህ ይነገረናል፦

"ወህኒ አዛዥ ወልደፃድቅ ይባላል፤ ባጤ ምኒልክ ዘመን ከነበሩ ገናና ባለስልጣኖች አንዱ ነበር፤ በዳግማይ ምኒልክ ዘመን የነፋስ በሽታ የሚባል የኮሌራ ወረርሽኝ ተነስቶ ብዙ ሰው ፈጅቶ ነበር፤ በወቅቱ ንጉስ ነገስቱ በሽታው ያልደረሰበት ቦታ በመምረጥ ከአዲስአበባ ወደ አንኮበር ወርደዋል ::
በጊዜው በምስራቅ የኢትዮጵያ ክፍል ግዳጅ ላይ የነበረው ወልደፃድቅ ምኒልክንና ለማግኘት ቀጠሮ ተይዞለት ስለነበር፤ ወደዚያው ጉዞ እንደጀመረ በበሽታው እንደተለከፈ ይረዳል :: ወድያው ራሱን ከሰው ነጥሎ ለመቆየት ወሰኖ እንደ ሽፍታ ወደ ዱር ገባ፤ የንጉሱ ዜና መዋእል የሆኑት አለቃ ገብረስላሴ በዘመኑ ፈሊጥ የፃፉትን ብጠቅስ፤
" ወህኒ አዛዥ ወልደፃድቅም በዲቤ ቆላ ጉበላ ክሚባለው አገር ሄዶ ከዱር ገብቶ በዳስ ተቀመጠ:: ነገር ግን ኩላሊት ያጤሰውን ልብ ያመላለሰውን
መርምሮ የሚያውቅ አምላክ እኔ ከሞትኩ ለማን ጌታ ይሆናሉ ሳይል ለጌታው ለአፄ ምኒልክ ማሰቡን አይቶ ከሞት አተረፈው" (ገፅ 150)"
ፈረንጆች “ኮረንቲን” ብለው የሚጠሩትን ነገር በባህላችን እንግዳ ነገር እንዳልነበረ ይህ የወልደፃድቅ ገጠመኝ ምስክር ይመስለኛል። ሰውየው ቤቱ መቀመጥ ሲችል ላካባቢው እንዳይተርፍ በማሰብ፤ ሰው የማይኖርበት እልም ያለ ዱር ውስጥ ገብቶ በዳስ መቀመጡ ይደንቃል። በሀኪም ሳይመከር፤ በሹም ሳይገደድ፤ በራሱ ፈቃድ፤ በሽታውን ወደ ዋናው መሪ ባስተላልፍ መንግስት ይፈርሳል በሚል ሰጋት ራሱን አግልሉዋል።"

እንግዲህ አጤ ምኒልክም ሆኑ ዘመኑ ለእምነት የነበረውን ቦታ መንገር ሰሚ ማድከም ነውና ትቼው መጠንቀቅ ከሰውነት ጠባይ ጋር በፀሎት ተሠናስሎ እንደሚያሻግረን አስታውሸ ልዝጋው።

በሰንደቃችን ቃሉን የሰጠን አምላክ እስኪጎበኘን ከክፋት ተጠብቀን እንቆየው።

።፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨፨
ይቆየን!